My Blog List

Friday, June 30, 2017

ኢትዮጵያ በፖሊሲ ዉለታ-ኣቅራቢዎች ገበያ


ሃገሬን የነ እንቶ-ፈንቶ ሃገር እላታለሁ። ምክንያቴ በርካታ ኣምዶችን የሚያጣቅስ ሲሆን በዚህ ኣጭር ፅሁፍ በፖለቲካ-ምጣኔሃብት ምህዋር በነጋ-በጠባ የምንታዘበዉን ቴክኒካዊ የእንቶ-ፈንቶነት ምልክቶችን በጥቂቱ እንመለከታለን።
እንደመቅድም ስለ ቋንቋ ኣጠቃቀማችንና በቅጡ ስለመግባባታችን በጥቂቱ እናንሳ። እንደሚታወቀዉ ሁሉ በኣንድ ሃገር የፖለቲካ፣ የምጣኔ-ሃብት፣ የማህበረሰባዊና የህግ መስተጋብር ውስጥ የቋንቋ ኣጠቃቀም ብቃትና ምጥቀት በርትእነት ለመግባባት የሚያበረክተዉ ልዩ ድርሻ በቀላል የሚታይ ኣይደለም። የኣማርኛ ቋንቋ የማዕከላዊ ኣስተዳደር (ወይም በተለመደዉ ሃረግ ‘የፌደራል መንግስት’) የሥራ መግባቢያ እንደመሆኑ፣ በተለይ በመገናኛ-ብዙሃን በኩል ከደቂቃን እስከ ልሂቃን ኣንደበት የምንሰማቸዉን ‘ሸዉራራ’ ቃላት ምን ያህል እያንሸዋረሩን ለመሆናቸዉ በማንሳት እንንደርደር። በርካታ ጥያቄዎችን ልናነሳ እንችላለን። ለኣብነት ያህል ስንቶቻችን በቁንጅናና በዉበት፣ በጭፈራና በእስክስታ፣ በክፍለ-ዘመንና በምእተ-ኣመት፣ በኣረጋዊና በኣንጋፋ፣ በየኔ-ቢጤና በነዳይ፣ በመንግስትና በኣስተዳደር፣ በኢኮኖሚ እድገትና ልማት፣ በባንዲራና በጨርቅ፣ በወያኔና በሽፍታ…(ወዘተርፈ) መካከል ያለውን ልዩነት የምናስተውል? በኣንድ ‘የኢትዮጵያ’ ቴሌቪዥን የዜና መስኮት መንግስት የሚለዉን ቃል እስኪታክተን ስንሰማ፤ “መንግስት እንዲህ ኣደረገ/ኣሰበ” ስንባል፤ ድርጊቱ የጠቅላይ ሚንስትሩን (ግለሰብ) ይወክላል ወይስ የኢህኣዴግን (ፓርቲ)፣ የሃገር ኣስተዳደሩን (ገቨርንመንት) ወይስ የሥራ ኣስፈፃሚዉን ኣካል (ኣድምንስትሬሽኑን)፣ የህዝብ ኣገልግሎት ተቋም ወይሰ የቀበሌ መስተዳድር? በዚህ ሁኔታ መንግስት ማለት ከቶ ማን ነዉ ብላችሁ ታዉቃላችሁ? በዘመናዊና ኢፊዉዳላዊ ሥርዓት ቃሉ በርግጥ ይህን ያህል የላላና ፈርጀ-ብዙ መሆን ኣለበትን?

የሳቅ-ጫሪዎቹ የቀልድ ጭብጥ?

የማንኛዉም ቋንቋ ውጣ-ውረድ ሂደት (ዳይናሚክስ) እንደተጠበቀ ሆኖ ማር የምትሰጠን ንብን ከሁለት ኣሰርት ኣመታት በኋላ በቄንጠኛ ስያሜ ‘ጥንዚዛ’ እያልን ብንጠራትና በስፋት ቢለመድ፣ ይህ ኣፈንጋጭ የስያሜ ለዉጥ በይፋ የተቀበልነዉ ካለመሆኑ የተነሳ በተለይም በኣዉሮፓና በሰሜን ኣሜሪካ የመሸጉትን ወገኖች ከጨዋታ ዉጭ ማድረጉ ኣይቀርም። ለኣስረጂነት ያህል ኣንድ የቅርብ ጓደኛዬ ምንጭ ጠቅሶ በቅርቡ ያጫወተኝን የሰሜን ኣሜሪካ የቀልድ-ቤት ዉሎ እንይ። የሳቅ-ጫሪዎቹ (ቀልደኞቹ) የመድረክ ላይ ቀልድ እያቀረቡ ነዉ። ኣብዛኛዎቹ ታዳሚዎች ከ20 ዓመታት በፊት ከሃገር የወጡ በመሆናቸዉ ቀልደኞቹ የሚያወርዱትን ቀልድ ኣደናጋሪ ይሆንባቸዋል። ሳቃቸዉን የሚለቁት ያደናገራቸዉ ቃል (ቃላት) ምን ማለት መሆኑን ኣጠገባቸዉ ካለ ሰዉ ጋር ከተወያዩና ከተግባቡ በኋላ ነዉ። የሳቅ-ጫሪዎቹ ቃላት በወያላና በመንደር ቃላት የተዋዙ፣ ይልቁንም ሸውራራ በመሆናቸዉ ነዉ ኣደናጋሪነታቸዉ።
ባጭሩ ሲቀመጥ፣ በምናቀርበዉ ማንኛዉም ሃሳብ ላይ ለማለት በፈለግነዉና በምንለዉ መካከል ያለዉ ልዩነት ቢያንስ መስፋት የለበትም ነዉ።
ኣብዮታዊና ልማታዊ ቃላት ከወያላና ከመንደር ሸዉራራ ቃላት ኣጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሃገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክን ዘወር ብለን ስንመለከት ከእያንዳንዱ የኣስተዳደር ሥርዓት ጋር የሚዘምኑ ቃላትን እየተቀበልን መምጣታችን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የዘዉዳዊዉን ሥርዓት ችላ እንበለዉና በደርግ ኣስተዳደር ዘመናት ባለሥልጣቱ ከሶሻሊስት ርእዮተ-ዓለም፣ ወይም ከኣብዮታዊ እብደታቸው ጋር የሚዛመዱትን እንደ ኣድሃሪ፣ ኣቆርቋዥ፣ የናት-ጡት-ነካሽ፣ ነጭ-ሽብር፣ ቀይ-ሽብር ከሚሉና ከመሳሰሉት ዘመነኛ ቃላት ጋር የተቆራኙ ነበሩ። የኢህኣዴግ ኣስተዳደር ባለሥልጣናትም በበኩላቸዉ ‘በኣብዮታዊና ዲሞክራሲ’ መንፈስ ታጅበዉ በርካታ ልዩ ቃላት ኣዘዉትረዉ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል ልማታዊ-ባለሃብት፣ ልማታዊ-መንግስት፣ ሙስና፣ ኪራይ-ሰብሳቢ፣ እና ኣሸባሪን መጥቀስ ይቻላል። እልፍ ስንልም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ፣ እና ህዝቦች በሚሉ ቃላቶች ላይ መሰረታዊ የፍቺ ለዉጥ እንመለከታለን። ኣብዛኛዎቹ ቃላት ለየት የሚያደርጋቸዉ ግን ኣደናጋሪና ለፖለቲካዊ ዉዥንብር በሚዉል መልኩ ከመቃኘታቸዉ በተጨማሪ በኣንዳንድ ቃላት ላይ ግልብ ቴክኒካዊ ጥፋት መፈፀማቸዉ ነዉ።
በዓለም-ኣቀፍ ደረጃም ተመሳሳይ የታሪክ ሰበዝ መምዘዝ እንችላለን። ምንም እንኳ በምልኣተ-ቅርፁ ከየትኛዉም የኢትዮጵያ መንግስት ኣስተዳደር ጋር ሊነፃፀር ባይችልም፣ በሃገረ ጀርመን በኣዶልፍ ሂትለር ይመራ የነበረዉ የናዚ ፓርቲ ኣስተዳደር ነባር ቃላቶችን በመጠምዘዝ፣ በመደቀል፣ ወይም ኣዲስ በመፍጠር ጀርመናዉያንን ለማደናገር ችሎ እንደነበር በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ።

የፖሊሲ ዉለታ-ኣቅራቢዎች ገበያ

በኢህኣዴግ ‘ሥርወ-ኣስተዳደር’ ዉስጥ ላለፉት በርካታ ዘመናት ከቀበሌ ኣስተዳዳሪ እስከ የተወካዮች ምክር ቤት ኣፈ-ጉባኤ የኣፍ ማሟሻ የሆነዉን “የኪራይ ሰብሳቢነት ኣመለካከት” ጉዳይ በኣደናጋሪነቱ ሚዛን በመድፋቱ ምክንያት ምንጩንና ኣላማዉን በዉን ልናጤነዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ። ቀዳሚ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ እንዳንቆለጳጰሱት ኣስተዳደራቸዉ “የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆነዉን ሙስናን” ለመዋጋት ማለሙንና ‘የልማት ሠራዊት’ መገንባት ኣስፈላጊ መሆኑን ኣሳውቀዉናል። እርግጥ ነዉ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በተቋም ደረጃም ከኢህኣዴግ የሥልጣን መቆናጠጥ ማግስት ጀምሮ ይታይ ነበር ቢባልም በግላጭ መንሰራፋት የጀመረዉ ግን ከ1990ዎቹ መባቻ ጀምሮ ለመሆኑ የሚያከራክር ኣይደለም። የኪራይ ሰብሳቢነት ኣደጋ መጋረጡን ለመጀመሪያ ጊዜ ያረዱን ደግሞ ኣይቀደሜዉ ኣቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ። ያኔ ልክ እንደ ኣሁኑ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት የገባዉ፣ ያልገባዉ፣ እንዲሁም የተደናገረ ህልቆ-መስፈርት ነበር። የፖለቲካ ጨዋታ በረቀቀ መልኩ የማይገባቸዉ ተራ ዜጎችን እንተዉና የከፍተኛ ምሁራን፣ የማእከላዊ ኣስተዳደር ኣስፈፃሚ ኣካል የካቢኔ ኣባላት፣ እንዲሁም ከተወካዮች ምክር ቤት ኣባላት ሰዎች መርጣችሁ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ኣስረዱን ብትሉ ከሞላ-ጎደል ሁሉም የተለያየና የተዛባ ኣረዳድና ምላሽ ማቅረባቸዉ ያልተለመደ ኣይደለም። ነገርግን ኪራይ-ሰብሳቢነት እና ሙስና ተመሳሳይ፣ ነገር ግን በመሰረታዊ ባህሪያቸዉ ለየቅል ስለመሆናቸዉ፣ አንዲሁም በኢህኣዴግና በባለሥልጣናቱ የተንሰራፋዉን የተሳሳተ የግንዛቤ ልዩነት ለማጥበብ እንሞክር።
የኪራይ ሰብሳቢነት ፅንሰ-ሃሳብ በ(.ኤስ.) ኣሜሪካ የፖለቲካና ምጣኔሃብት ምህዋር ለመጀመሪያ ጊዜ ጎልቶ እንዲወጣ ካደረጉት ዉስጥ ጎርዶን ቱሎክ የተባሉ የስነ-ምጣኔሃብት መምህር ሲሆኑ በርሳቸዉ ኣገላለፅ ኪራይ ሰብሳቢነት በግል ወይም በቡድን ደረጃ የመንግስት ኣስተዳደርን ወይም ባለሥልጣናትን በማባበል፣ በመደለል፣ ወይም በማስገደድ በግብር፣ በቀረጥና በልዩ ልዩ የመንግስት ወጪዎች ኢፍትሃዊ ጫና መፍጥር፤ እንዲሁም ቀያጅ ህግ፣ ደንብ፣ ወይም መመሪያ በማዉጣት የተለየ የገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም [ለምሳሌ ሥልጣን ‘ማስቀጠል’] ለማግኘት የፖለቲካዊ-ምጣኔሃብቱን የጨዋታ ሜዳ ኪራይ-ሰብሳቢዎቹን በሚጠቅም መልኩ መቃኘት መቻል ማለት ነዉ።
ከኢትዮጵያ ፀሃይ በታች በኪራይ ሰብሳቢነት ዙሪያ የፃፈ፣ ያስተነተነ፣ የሞገተ እምብዛም ኣለ ለማለት ባንደፍርም ጥቂቶች ግን ኣልጠፉም። በመቐለ ዩንቨሲቲ የህግና ስነ-መስተዳድር ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት/የነበሩት ሃብታሙ ኣለባቸዉ የኢትዮጵያን የኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ ከምእራብያኑ ተጨባጭና መስተጋብራዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣቀስ ለሃገራችን ተስማሚ ነው ያሉትን የፅንሰ-ሃሳብና ተግባራዊ ሰበዞችን መዘዋል። በርሳቸዉ ኣስተያየት የሃገራችን የማህበራዊ ንቃተ-ህሊና ደረጃና በግብኣተ-ምርት ኣጠቃቀም ዙሪያ ላይ በማተኮር የፖለቲካ ሥርዓቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ስለሆነም በኛ ሃገር ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከተዉ የኪራይ-ሰብሳቢነት ኣባዜ በግል ደረጃ ሊፈፀም የሚችለዉ ከሃገሪቱ ርእሰ-መስተዳድር ጀምሮ በሚንስትሮች፣ በየክልሎቹ ርእሳነ-መስተዳድር፣ በጦር ሃይል የበላይ መኳንንት፣ እና በፖሊሲ ደረጃ ተፅእኖ ፈጣሪ በሆኑ ግለሰቦች ሲሆን በቡድን ደግሞ በገዢዉ ፓርቲና በዉስጡ በሚገኙት ኣንጃዎቹ፣ ተቋማት፣ እንዲሁም ያልተገባ ጥቅምን በሚያሳድዱ ቡድኖች ነዉ። የኪራይ ሰብሳቢነት ኣመለካከትና ተግባር በቀበሌ መስተዳድር ሰራተኛ ከሚፈጠር ተራ ምግባረ-ብልሹነትና ጉቦኝነት፣ እንዲሁም ስግብግብ ባለሃብቶች ከሚፈፅሙት ደንብ መተላለፍና ወንጀል ጋር እያደበላለቁ መደናገር ኣንድም ጉዳዩን በውን ካለመገንዘብ፣ ኣልያም በፖለቲካ ሥርዓቱ ልሂቃን በሚገባ የታሰበበትና የወል ድንቁርና ለመፍጠር ያለመ ሊሆን እንደሚችል መገመት ኣያዳግትም። ልክ-ልካችን እንነጋገር ከተባለ ችግራችን በዉኑ ኣሳፋሪ ነው።

ሥርዓቱ ራሱ ኪራይ-ሰብሳቢ ነዉ

በሃገራችን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም ኣወንታዊ ብቃታቸዉን ኣሳይተዋል ተብለው የሚቆጠሩት ኣቶ መለስ ዜናዊ ለኪራይ-ሰብሳቢነት ፅንሰ-ሃሳብ ያላቸዉ ኣረዳድ ያፈነገጠ ነዉ። ለማስተርስ ዲግሪ ትምህርታቸዉ መቋጫ የተዘጋጀና በጅማሮ በቀረዉና "የኣፍሪካ ልማት፦ የተዘጉ መንገዶችና ኣዳዲስ ጅማሬዎች" የሚል ርእስ የያዘው ጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዳመለከቱት የግሉ የንግድ ሥራ ማህበረሰብ ከውጭ ዓለም ጋር ተወዳድሮ እውነተኛ እሴት መፍጠር ባለመቻሉ ምክንያት፣ ያለው ኣማራጭ ከተፈጥሮ-ሃብት፣ ከእርዳታ፣ እንዲሁም ከፖሊሲ ኪራይ በመሰብሰብ ሃብት ማካበት መርጧል ይላሉ። ስለሆነም መንግስት ወይም የመንግስት ኣስተዳደር ያለ ተቀናቃኝ ሥልጣን በመጠቅለል የግሉን ዘርፍ መምራት ያስፈልገዋል ሲሉ ሞግተዋል። ሃሳባቸው ባጭሩ ሲታይ የኪራይ-ሰብሳቢነት ተቃራኒ እሴት-ፈጠራ ነዉ ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል።
በኣንፃሩ፣ በፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሳይንስ ኣረዳድ ረገድ፣ የኢትዮጵያ ኪራይ-ሰብሳቢነት ችግር በተጭባጭ ክስተቶች እንዲህ ሊገለፅ ይችላል።
በግርምት እንደምናስታውሰዉ የፖለቲካዉን መዘውሩን ከሁለት ኣሰርት ኣመታት በላይ ጨምድደዉ የያዙት ‘ሙሉእ-በክልኤዉ’ ኣቶ መለስ ዜናዊ የባለስልጣኖቻቸውን የሹመት መስፈርት ሲያስተነትኑ ‘ታማኝነት’ ዋናውና ቀዳሚዉ መመዘኛ ነበር። የሹማምንቱ ታማኝነታቸው ለሰዉ ልጅ ነፃነት፣ ለፍትህ፣ ለሃገርና ለህግ ልእልና፣ ለዲሞክራሲ፣ ይልቁንም ለህሊናቸዉ ሳይሆን ለቆሌኣቸዉ፣ ከዚያም ሲያልፍ በኣምሳላቸውና በኣይነታቸው ልክ ለገነቡት ‘የኣሳማ-እርሻ ህገ-መንግስት’ መሆኑን ኣስረግጠዉልን ነበር። በዚህ ረገድ ኣብነት እናንሳ ካልን የሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲዉን ተልእኮና ኣላማ ስናጤን በመንግስት የኣስተዳደር መዋቅሮች ለሚመደቡ ታማኝ ሹማምንቶች ማሰልጠኛ ይሆን ዘንድ በፖሊሲ ደረጃ ታምኖበት የተዋቀረ የኪራይ-ሰብሳቢነት ማሽን መሆኑን እንገነዘባለን።
በኢኮኖሚው መስክ ደግሞ ስንመለከት በርካታ የኪራይ ሰብናቢነት መዘዉሮችን እንመለከታለን። በማህበረሰብ መልሶ-ማቋቋሚያነት ተጠንስሰዉ፣ ነገር ግን ከህግ ኣንፃር በኢህኣዴግ ባለሥልታናት ሥምና በሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተመዘገቡትና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙትን የኢህኣዴግ ኩባናንያዎች ጉዳይ እናንሳ። ለኣብነት ያህልም የትግራይ የመዋእለ-ንዋይ (ኢንቨስትመንት) ፍስት ከ80 በመቶ በላይ ድርሻ ጨምድዶ ለበርካታ ኣመታት የተቆጣጠረዉና ‘ትእምት’ እየተባለ የሚጠራዉን የኩባንያዎች ስብስብን ኣቅርበን እንመልከት። ትእምት በህወሓት ባለሥልጣናት የሚተዳደር፣ ወጪና ገቢዉ ተመርምሮ የማያዉቅ፣ ለህወሓትን ዘለቄታዊ ዙፋን ማስቀጠያ ዘመቻዎቸ የሚደጉምና ለባለሥልጣናቱ የኑሮ ማንደላቀቂያነት የሚያገለግል፤ ባለሥልጣናቱ በገንዘብ ክፍፍል ሳይስማሙ ሲቀሩ ሽጉጥ የሚማዘዙበት፣ እዉነተኛ ባለቤት የሌለዉ ኣሻንጉሊት ድርጅት ነዉ።
በህግ ድጋፍ የታጀበዉ የትእምት ታሪክ የግልና የቡድን ያልተገባ ጥቅም ማስጠበቁ ኣንድ የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ሆኖ፣ በዚህ የመዋእለ-ንዋይ ምህዳር ባለሥልጣኖቻችን ምን ፅድቅ ቢታሰባቸዉ ነዉ የግል ኩባንያዎችን ከኢህኣዴግ ኩባንያዎች ጋር እኩል የሚያስተዳድር ፖሊሲ የሚቀርፁትና የሚያስፈፅሙት? እነዚህ ኩባንያዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በማእከላዊና የክልል ኣስተዳደሮች ልዩ የፖሊሲና የተግባር ድጋፍ ስለሚሰጣቸው ‘የተንጠልጣይነት’ ወይም የክሮኒዝም ተጠቃሚዎች ያደርጋቸዋል። ለኢትዮጵያችን የተሰላ ኣሃዝ ባይኖርም የዘኢኮኖሚስት መፅሄት የምጣኔ-ሃብት ምርመራ ህዋስ በተለያዩ ሃገራት ያካሄደዉ ጥናት እንደሚያመለክተዉ ከኪራይ-ሰብሳቢነት ባሻገር በርካታ የኣለማችን ኢኮኖሚዎች በተንጠልጣይ ኩባንያዎች የተሞሉ ናቸዉ። በዚህም መሰረት 18 በመቶ የሩሲያ ኣመታዊ ምርት ከክሮኒዝም ተጠቃሚዎች የመጣ እንደሆነ ያስተነትናል። በተመሳሳይ መልኩ በዩ.ኤስ. ኣሜሪካ የሁለቱም የቡሽ ኣስተዳደሮች በሃሊበርተን ኩባንያ በኩል የፈፀሙትን የኪራይ ሰብሳቢነት ታሪክ ለንፅፅር ያህል ማጣቀስ ኣስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
ይህን ሁሉ ፅልመታዊ የዓለም ክስተት በኣጭሩ እንደምን መግለፅ ይቻላል? የሃቫርድ ዩንቨርሲቲዉ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ መምህር ዳኒ ሮድሪክ በተዛማጅ ርእሱ‘ቀማኛ የፖለቲካ-ምጣኔሃብት ሥርዓት’ በተሰኘ የተባ ፅሁፋቸዉ እንዳስቀመጡት ፖለቲከኞች ሃብት ኣጋባሽ የፖሊሲ ዉለታ ኣቅራቢዎች ሆኑ፤ ዜጎች የኪራይ-ሰብሳቢነት ደላሎች እና የልዩ ጥቅም ኣሳዳጆች ሆኑ፤ የፖለቲካ ስርዓቱ እንዲሁ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ማግኛ ሲባል የምርጫ ድምፅና የፖለቲካ ተፅእኖ መገበያያ ማእከል ሆነ” ብለዋል።

ተጨማሪ ኣንደምታዎች

ከኪራይ-ሰብሳቢነትና ተንጠልጣይነት ችግር ባሻገር በኢትዮጵያ የፖለቲካ-ምጣኔሃብት ሥርዓት ላይ ተጨማሪ ጠቃሚ ጥያቄዎችን እንድናነሳ እንገደዳለን። ፈራ፣ ተባ እያላችሁም ቢሆን ጠይቁ። በዚች ሃገርየመንግስት ኣስተዳደር’ መጠንና ልክ ምን ያህል ነዉ? ምን ያህልስ መሆን ኣለበት? ይህ ኪራይ-ሰብሳቢነትን ተክሎና ኮትኩቶ ያሳደገ ሥርዓት በኣንዳች ‘ተዓምር’ ቢንኮታኮት ምን ሊፈጠር ይችላል? ለዉጥ መቋቋም የሚችል የሥነ-ልቦና ዝግጅት ኣለን? የፖለቲካዉን መዘዉር የያዙት ኢህኣዴግና ባለሥልጣናቱ ከትጥቅ ትግል ዘመናት ጀምሮ የሰሩት ወንጀል (የጅምላ ጭፍጨፋና ሃገር ክህደትን ያካትታል) በኣንድ ወገን ይዘን፣ የ‘ሲቪል’ ባለስልጣናትና ከፍተኛ የጦር መኳንንቱ በግል ደረጃ የቆለሉት ያልተገባ ሃብት ከኪራይ ሰብሳቢነት ባህል ጋር ምንና ምን ናቸው? እነኚህ የጥያቄ መላምቶች፣ ተረት-ተረት ወይም ኣልቧልታ ኣይደሉም፤ መነሳት ያለባቸዉ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸዉ።
ሌላም ወሳኝ ጉዳይ ኣለ። ቢያንስ ላለፉት 23 ዓመታት በፅኑ የጥራዝ-ነጠቅ ባህል ላይ የተገነባችዉ ኢትዮጵያዬ ዕዳዋ እንዲህ የዋዛ ኣይደለም። በታዋቂዉ የጊርት ሆፍስቴድ የብሄራዊ ባህል ትንተና መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ ለመስራት የሚኖር፣ በተቀናቃኝነት የሚወዳደር፣ ሃብት ለማካበት የሚጥር፣ መፃኢ-ጊዜን በፍርሃትና በጥርጣሬ የሚያይ በሚል ይገልፃታል። ኣንድ ሰዉ የህዝብን ሃብት በጠራራ ፀሃይ በመዝረፉ “የድርሻዉን ወሰደ” ተብሎ የሚሞገስበት ሃገር በምን ጥበብ ነዉ ሙስናን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን የምናጠፋዉ? ኪራይ-ሰብሳቢነት ከግልና ከቡድን ሴራ ኣልፎ ብሄራዊ (ኣገር-ኣቀፍ) ባህል ሆኗል እኮ። ሥርዓቱ ራሱ ኪራይ-ሰብሳቢ ነዉ። ዓለሙ ‘በሙሉ’ ኪራይ-ሰብሳቢ ነዉ።
የኔ-ቢጤ (ወይም የናንተ-ቢጤ) ቀናኢ ይህችን የነ እንቶ-ፈንቶ ሃገርን ለመታደግ ሙሉ ጊዜዉን ቢሰዋ፣ ከልማዳዊዉ የፖለቲካ ሽፍታነት ፀድቶ በእዉነትና ስለ እዉነት ኖሮ በፅኑ መሰረት ሊገነባት ምኞትና ወኔው ቢኖረዉም ድካም ይታሰበዋል። የድካሙ ምንጭ ደግሞ እንደጅብራ ፊቱ ላይ የተገተረዉ የወል ማሃይምነት ነዉ።

Tuesday, March 14, 2017

ያገሬ ሰዉ በድራገኑ-ዓለም ዋዜማ


በዩ.ኤስ. ኣሜሪካ የመገናኛ–ብዙሃን መድረክ ታዋቂ የሆኑት ፋሪድ ዘካሪያ 'የድህረ–ኣሜሪካ ዓለም' በተሰኘ የ2008 መጽሃፋቸዉ የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ የከባድ ሚዛን ጨዋታ መሪነት ከምእራቡ ሃያላን፣ በተለይም ከኣሜሪካ፣ ወደ ምስራቁ እንደሚያዘም ኣስተንትነው ነበር። ይህ ትንበያ በስታቲስቲካዊ መረጃና በተጨባጭ ኣመላካች ሂደቶች በመደገፉ ምክንያት ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ሌሎች ፀሃፍትም እንዲሁ ይህንን የሃይል ሚዛን ኣዝማሚያ በሚያጠናክር መልኩ ተቀባብለውታል። ማርቲን ጃክ የተባሉ ፀሃፊ 'ቻይና ዓለምን በምትገዛበት ጊዜ' የሚል ርእስ በያዘው መፅሃፋቸው እ... 2050 የቻይና ምጣኔ-ሃብት የኣሜሪካኑን እስከ እጥፍ በሚደርስ መጠን (70 ትሪሊዮን ዶላር) እንደሚያስከነዳ በማስተንተን ከብሉይ ወደ ኣዲስ የዓለም ሥርዓት መሸጋገራችን ኣይቀሬ መሆኑን ያስረግጣሉ።
ከቅርብ ዘመናት ወዲህ እየተንሰራፋ የመጣው የሲኖ–ኣፍሪካ የምጣኔ–ሃብት ትስስር ቻይና ከምታካሂዳቸው በርካታ የመሰረተ–ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ባሻገር ማእድናትን በማሰስና በማውጣት የኣህጉሪቷን ሃብት እየተጠቀመችበት ትገኛለች። 'የቤጂንግ ስምምነት' በሚል የቅፅል-ስሙ የሚታወቀው የቻይና የንግድ ዲፕሎማሲ መርህ ኣፍሪካ ከኣውሮጳ ጋር የነበራትን የቅኝ-ግዛት፣ ብሎም የጅኣዙር-ቅኝ-ግዛት (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) ኣይነት ግንኙነት ላይ የተመረኮዘ ነዉ ተብሎ ይፈረጃል። ይህም ኣፍሪካ ጥሬ-እቃዋን፣ ቻይና ደግሞ ያለቀለትን ምርት በመላክ ይተሳሰሩ እንጂ ኣፍሪካ በኢኮኖሚያውዉ ሆነ በማህበራዊ መስክ እምብዛም ለውጥ ኣላመጣችበትም።
በንግድና የኢንቨስትመንት ዙሪያ እ... 2000 ቻይና በኣፍሪካ ካፈሰሰችዉ የ10 ቢሊዮን ዶላር መዋእል-ንዋይ በ2009 እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። በ2016 ይህ ኣሃዝ እጅግ ኣሻቅቦ ታይቷል። በኣወንታዊ ጎኑ ሲታይ የቻይና ንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ-ኣጥነትን በመቀነስና የተጓዳኝን ሃገርን ኣቅም በመገንባት የሚትሰጠው ጠቀሜታ በኣንድ በኩል ይዘን፣ በልገሳ እና በብድር የምታቀርባቸው ኣማራጮች እንዲህ በቀላል የሚታዩ ኣይደሉም። በተጨማሪም በተለያየ ኣግባብ የሚሰበሰብ የመንግስት ገቢ ጠቃሚ መሆኑ የማይካድ ነዉ።
ነገርግን ቻይና በሰብኣዊ መብት ረገጣ፣ በኣካባቢ ብከላ፣ እንዲሁም በብሄራዊ ባህል መላሸቅ የምታበረክተው ኣሉታዊ ኣስተዋፅኦ እጅግ ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዓለም-ኣቀፉ የሰብኣዊ መብት ተመልካች ዘገባ መሰረት እ... 2011 በዛምቢያ የማእድን ሰራተኞች ላይ ተፈፅሟል ያለዉን የሥራ ደህንነት ጉድለቶች እጅግ ዘግናኝ ሲል ይገልፀዋል። ከዓለም-ኣቀፍ እና ከሃገሪቱ የሰራተኛ መብቶች መጠበቂያ መርሆችና ህግጋቶች ኣንፃር ሲታይ ቅጥ-ያጣ መተላለፍ ይፈፀማል ብሎ ያስቀመጣቸዉ ኣብነቶች ደግሞ በርካታ ናቸዉ። ለምሳሌ ያህል ቻይናዎቹ በመዳብ ማእድን የማውጫ ጉድጓድ (ወይም ዋሻ) ዉስጥ የፈነዳ ደማሚት ሳይረጋ (ወይም በጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ) ሰራተኞችን ያለምንም መከላከያ ወደ ጉድጓዱ እንዲገቡ ያስገድዳሉ። በመሆኑም ዜጎች ለተለያየ በሽታዎች፣ ይልቁንም ለሳምባ ካንሰር ይጋለጣሉ። ይህም ኣንሶ በቀን እስከ 18 ሰዓት፣ በኣመት ደግሞ እስከ 365 ቀናት ያለ እረፍት እንዲሰሩ በማስገደድ ወደ ባርነት ኣገዛዝ ይመልሷቸዋል ። ይህን ህገ-ወጥ ተግባር የጠቆመ ወይም ያሳወቀ ደግሞ ከሥራ ይባረራል።
በጥቅሉ ሲታይ የቻይና ኩባንያዎች የሚፈፅሙት የግፍ ኣይነት በዛምቢያ የተወሰነ ኣይደለም። በቻይናም ኣለ፤ በኢትዮጵያም በኣንፃራዊ መልኩ ይታያል። የቻይናዎቹ የሥራ መርህ 'በሰዉ ህይወትና በምርታማነት ላይ የቱንም ያህል ወጪ ይኑር ውጤት ማስመዝገብ ኣለብህ' ይመስላል።
እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ተመዝግበው በኣመዛኙ በቴሌኮምና ትራንስፖርት የመሰረት-ልማት ግንባታ፣ እንዲሁም በማእድን ማውጣት ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ምድር-ባቡር ኮርፖሬሽን (...) ባለቤትነት እና በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (....) የሥራ ተቋራጭነት የሚካሄደው የወልድያ(ሃራገበያ) – መቐለ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው።
በኢ... የፕሮጀክቱ ሥራ ኣስኪያጅ ኣቶ ገብርመድህን ገብረኣሊፍ በቅርቡ ለመገናኛ-ብዙሃን እንደገልፁት የፕሮጀክቱ ስኬታማነት 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን የባቡር መጓጓዣ ሲጀምር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መስተጋብር ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ኣብራርተዋል። በተቋራጩ ኩባንያ ለተቋቋሙት ሰባት የማስተባበሪያ ቀጣናዎች እና በትግራይ ክልል በራያ-ዓዘቦ ወረዳ መቻረ ሜዳ ላይ የሚገኘው ኣንድ ዋና መስሪያ-ቤት በኣካባቢ ሚሊሻዎች፣ በመደበኛ ፖሊስ፣ እንዲሁም በፌደራልና በክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል ይጠበቃል። ፖሊሶቹ ልዩ ኣበል እየተከፈላቸዉ የጥበቃና የደህንነት ሥራ የሚያከናዉኑ ሲሆን በመብት ጥያቄና በተራ ኣምባጓሮ በሚፈጠሩ ግጭቶች ባገርቤት ዜጎች ላይ የድብደባና የማዋከብ በደል እንደሚፈፅሙ በርካታ የኣይን እማኞች ይገልፃሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቋራጩ ኩባንያ በተለይ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የፖሊስና የፀጥታ ባለሥልጣናት ዪፋዊ ያልሆነ ጉርሻ እንደሚሰጥ ሥማቸዉ ሊጠቀስ የማይፈልጉ የዉስጥ-ኣዋቂ ምንጮች ይጠቁማሉ።
ባገርቤት ሠራተኞች ላይ የሚፈፀም ግፍ ፈርጀ–ብዙ ነዉ። ለማስረጃነት ያህል ያነጋገርኳቸው የመብት ተጠቂዎች እንደተናገሩት ከሆነ የሠራተኛና ኣሰሪ ግንኙነት የጌታና የሎሌ የሆነ ያህል በንቀትና በስድብ የታጀበ ነዉ። የማዕድ ቤት ሰራተኞች ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ በቀን ከ16 ሰዓታት ላላነሰ ጊዜ ይሰራሉ። ለተቋራጩ ኩባንያ የፕሮጀክት የበላይ ኃላፊዎች የወሲብ ምቾት የሚተጉ ቆነጃጅት በኣዋሳቢዎች ይደለላሉ፤ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ከሥራ እስከ መባረር የሚደርስ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በቴክኒክ የሥራ መደብ የተቀጠሩ ሠራተኞች ሽንት ቤት እንዲያፀዱ ይገደዳሉ። ከሠራተኞች ደሞዝ ኣከፋፈል ጋር በተያያዘም በዘፈቀደ የተሰላ የሂሳብ ማጭበርበር እንደሚፈጸም ኣንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከኣፋር ክልል የተወከሉ የማህበራዊ ዋስትና ባለሥልጣን ቡድን በቅርቡ የመስክ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ኣንዷ የቡድኑ ኣባል ወይዘሮ እንባንቸዉን መቆጣጠር እያቃታቸዉ በኣይናቸው ያዩትን የህግ ጥሰት ኣጫዉተዉኛል። የቡድኑ ተልእኮ የኣገር-ቤት ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና መብት ምን ያህል ስለመከበሩ ማጣራት ነበር። እጅግ በርካታ ሠራተኞች የጥሮታ ዋስትና ማመልከቻ ቅፅ ኣልሞሉም ብቻ ሳይሆን ማህደር የተከፈተላቸውም ቢሆኑ ገንዘብ ፈሰስ ኣልተደረገላቸዉም። የቡድኑ ኣባላት እግረ-መንገዳቸዉን የዋስትና ማመልከቻ ቅፅ ማስሞላት ነበረባቸዉና ሠራተኞችን ኣንድ-በኣንድ እየጠሩ በማስሞላት ላይ እያሉ ቻይናዊው ኣለቃ ቅፅ በመሙላት ላይ ያለን ሰራተኛ በጥፊና በርግጫ እያጣደፈ ከወሰደዉ በኋላ ወዲያዉኑ ከሥራ ኣባርሮታል። "እንዲህ ኣይነት ግፍ በሃገራች እንዴት ይፈፅማሉ? ምን ያህል ቢንቁን ነዉ?” ሲሉ በኣንክሮ ይጠይቃሉ ወይዘሮዋ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሠራተኞች የመብት ጥያቄ ኣላነሱም ማለት ኣይደለም። ከተለያዩ ወረዳዎች የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳዉ ኣንድ ዓመት ከመንፈቅ በሆነ ጊዜ ዉስጥ የተቋራጩ ኩባንያ ከ500 የማያንሱ የመብትና የይገባኛል የክስ ጉዳዮችን ኣስተናግዷል። በተለይ የባቡር ሃዲዱ በሚያልፍባቸዉ የትግራይ ወረዳዎች የመብት ረገጣው የከፋ ብቻ ሳይሆን በህጉ መሰረት ለሰራተኞች መብት የፈረዱ ዳኞች በሌላ እንዲተኩ ተደርጓል የሚል ስሞታም ኣለ።
ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ ኣንፃር ከተቋራጩ ኩባንያ ወገን ስለዚህ የመብት ረገጣ ኦፊሴላዊ ኣስተያየት መጠየቅ ተገቢ ነዉ። ነገርግን ከንቱ ድካም ነው። እንኳንስ በመገናኛ-ብዙሃን ለሚወጣ ኣስተያየት፣ ይላሉ ኣንድ ኣስተያየት ሰጪ፣ በመደበኛ የሥራ ሂደት ላይ ካገርቤት ሠራተኛ ጋር የሚደረግ ማንኛዉም የመረጃ ልዉዉጥ መደበኛዉን የኣሰራር ሂደት የተከተለ ኣይደለም። ስለዚህ እንዲያዉ ዝም ነዉ። ለንፅፅር ያህል በቱርክ ኩባንያ 'ያፒ መርከዚ' በተያዘዉ ተመሳሳይ የምድር ባቡር ፕሮጀክት (አዋሽ – ሃራገበያ) ያለዉን ሁኔታ መዳሰስ ጠቃሚ ቢሆንም በዚህ ዘገባ ኣልተካተተም።
ኣሁን ምን 'ይጠበስ'?
ስለ የህግ የበላይነት፣ የዜጎች ደህንነት እና ስለ ብሔራዊ ሥነ–ምግባራችን የምንቆረቆር ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ኣንገብጋቢው ጉዳይ ይህ የመብት ጥሰት ብቻ ኣይደለም። ኢትዮጵያ ለፈረመችባቸዉ ዓለም-ኣቀፍ የሰብኣዊና የሰራተኞች መብት ስምምነቶች ፣ እንዲሁም በይፋ ላወጀችዉ የሰራተኛና ኣሰሪ ኣዋጅ 397/2003 ከቁብ የማይቆጥር ኢፍትሃዊ የሰዉ ኃይል ኣስተዳደር ሥርዓት በጠራራ ፀሃይ መተግበሩ ነዉ።
በኢትዮጵያ ምድር ይህ ሁሉ የመብት ረገጣ ሲፈፀም የህግ ዉክልና የተሰጣቸዉ በየደረጃዉ ያሉ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች፣ የፖሊስና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ለምን ድምፃቸውን ኣጠፉ? የሴራ መላምት እንጎንጉን ከተባለ ከቻይና የሥራ ባህል ኣንፃር እንደ ተራ ምግባረ-ብልሹነት የሚቆጠረዉ ጥቃቅን ሙስና (ፔቲ ኮረፕሽን) ተካሂዷል፣ ጉቦ ወይም ጉርሻ ተከፍሏቸው ሊሆን ይችላል ብለን መነሻ ልንይዝ እንችላለን። ይሁንና ተጨባጭ ምርመራ ያስፈልገዋል።
በጥቅሉ ሲታይ ግን ኢትዮጵያ የዉጭ-ቀጥታ-ኢንቨስትመንት በምታስተናግድበት ጊዜ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ለሚፈጥሩት ተፅእኖዎች መከላከያ ኣስቀድማ መላ መዘየድ ይገባታል። በደቡባዊ-እስያ ባሉ ሃገራት የተፈፀመዉን ኣይነት ወንጀል፣ ብዝበዛና ሥርዓት – ኣልበኝነት ለመከላከል የሚመለከታቸው በህግ ሥልጣን የተሰጣቸዉ ሁሉ ቅጥ ያለዉ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር ይገባቸዋል። በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (....) የተፈፀመዉና እየተፈፀመ ያለው ግፍ በተመለከተ ግን ኣስቸኳይና ዪፋዊ ምርመራ ተደርጎበት የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ ኣለበት። ኣልያም እንደነዚያ ተስፋቸዉ የተሟጠጠባቸው ያገሬ ሰዎች በዝምታ መቆዘም ከተመረጠ ቻይና ኢትዮጵያን በእጅ–ኣዙር ቅኝ እንደያዘች ልንቆጥረዉ እንችላለን።