My Blog List

Tuesday, March 14, 2017

ያገሬ ሰዉ በድራገኑ-ዓለም ዋዜማ


በዩ.ኤስ. ኣሜሪካ የመገናኛ–ብዙሃን መድረክ ታዋቂ የሆኑት ፋሪድ ዘካሪያ 'የድህረ–ኣሜሪካ ዓለም' በተሰኘ የ2008 መጽሃፋቸዉ የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ የከባድ ሚዛን ጨዋታ መሪነት ከምእራቡ ሃያላን፣ በተለይም ከኣሜሪካ፣ ወደ ምስራቁ እንደሚያዘም ኣስተንትነው ነበር። ይህ ትንበያ በስታቲስቲካዊ መረጃና በተጨባጭ ኣመላካች ሂደቶች በመደገፉ ምክንያት ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ሌሎች ፀሃፍትም እንዲሁ ይህንን የሃይል ሚዛን ኣዝማሚያ በሚያጠናክር መልኩ ተቀባብለውታል። ማርቲን ጃክ የተባሉ ፀሃፊ 'ቻይና ዓለምን በምትገዛበት ጊዜ' የሚል ርእስ በያዘው መፅሃፋቸው እ... 2050 የቻይና ምጣኔ-ሃብት የኣሜሪካኑን እስከ እጥፍ በሚደርስ መጠን (70 ትሪሊዮን ዶላር) እንደሚያስከነዳ በማስተንተን ከብሉይ ወደ ኣዲስ የዓለም ሥርዓት መሸጋገራችን ኣይቀሬ መሆኑን ያስረግጣሉ።
ከቅርብ ዘመናት ወዲህ እየተንሰራፋ የመጣው የሲኖ–ኣፍሪካ የምጣኔ–ሃብት ትስስር ቻይና ከምታካሂዳቸው በርካታ የመሰረተ–ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ባሻገር ማእድናትን በማሰስና በማውጣት የኣህጉሪቷን ሃብት እየተጠቀመችበት ትገኛለች። 'የቤጂንግ ስምምነት' በሚል የቅፅል-ስሙ የሚታወቀው የቻይና የንግድ ዲፕሎማሲ መርህ ኣፍሪካ ከኣውሮጳ ጋር የነበራትን የቅኝ-ግዛት፣ ብሎም የጅኣዙር-ቅኝ-ግዛት (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) ኣይነት ግንኙነት ላይ የተመረኮዘ ነዉ ተብሎ ይፈረጃል። ይህም ኣፍሪካ ጥሬ-እቃዋን፣ ቻይና ደግሞ ያለቀለትን ምርት በመላክ ይተሳሰሩ እንጂ ኣፍሪካ በኢኮኖሚያውዉ ሆነ በማህበራዊ መስክ እምብዛም ለውጥ ኣላመጣችበትም።
በንግድና የኢንቨስትመንት ዙሪያ እ... 2000 ቻይና በኣፍሪካ ካፈሰሰችዉ የ10 ቢሊዮን ዶላር መዋእል-ንዋይ በ2009 እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። በ2016 ይህ ኣሃዝ እጅግ ኣሻቅቦ ታይቷል። በኣወንታዊ ጎኑ ሲታይ የቻይና ንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ-ኣጥነትን በመቀነስና የተጓዳኝን ሃገርን ኣቅም በመገንባት የሚትሰጠው ጠቀሜታ በኣንድ በኩል ይዘን፣ በልገሳ እና በብድር የምታቀርባቸው ኣማራጮች እንዲህ በቀላል የሚታዩ ኣይደሉም። በተጨማሪም በተለያየ ኣግባብ የሚሰበሰብ የመንግስት ገቢ ጠቃሚ መሆኑ የማይካድ ነዉ።
ነገርግን ቻይና በሰብኣዊ መብት ረገጣ፣ በኣካባቢ ብከላ፣ እንዲሁም በብሄራዊ ባህል መላሸቅ የምታበረክተው ኣሉታዊ ኣስተዋፅኦ እጅግ ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዓለም-ኣቀፉ የሰብኣዊ መብት ተመልካች ዘገባ መሰረት እ... 2011 በዛምቢያ የማእድን ሰራተኞች ላይ ተፈፅሟል ያለዉን የሥራ ደህንነት ጉድለቶች እጅግ ዘግናኝ ሲል ይገልፀዋል። ከዓለም-ኣቀፍ እና ከሃገሪቱ የሰራተኛ መብቶች መጠበቂያ መርሆችና ህግጋቶች ኣንፃር ሲታይ ቅጥ-ያጣ መተላለፍ ይፈፀማል ብሎ ያስቀመጣቸዉ ኣብነቶች ደግሞ በርካታ ናቸዉ። ለምሳሌ ያህል ቻይናዎቹ በመዳብ ማእድን የማውጫ ጉድጓድ (ወይም ዋሻ) ዉስጥ የፈነዳ ደማሚት ሳይረጋ (ወይም በጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ) ሰራተኞችን ያለምንም መከላከያ ወደ ጉድጓዱ እንዲገቡ ያስገድዳሉ። በመሆኑም ዜጎች ለተለያየ በሽታዎች፣ ይልቁንም ለሳምባ ካንሰር ይጋለጣሉ። ይህም ኣንሶ በቀን እስከ 18 ሰዓት፣ በኣመት ደግሞ እስከ 365 ቀናት ያለ እረፍት እንዲሰሩ በማስገደድ ወደ ባርነት ኣገዛዝ ይመልሷቸዋል ። ይህን ህገ-ወጥ ተግባር የጠቆመ ወይም ያሳወቀ ደግሞ ከሥራ ይባረራል።
በጥቅሉ ሲታይ የቻይና ኩባንያዎች የሚፈፅሙት የግፍ ኣይነት በዛምቢያ የተወሰነ ኣይደለም። በቻይናም ኣለ፤ በኢትዮጵያም በኣንፃራዊ መልኩ ይታያል። የቻይናዎቹ የሥራ መርህ 'በሰዉ ህይወትና በምርታማነት ላይ የቱንም ያህል ወጪ ይኑር ውጤት ማስመዝገብ ኣለብህ' ይመስላል።
እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ተመዝግበው በኣመዛኙ በቴሌኮምና ትራንስፖርት የመሰረት-ልማት ግንባታ፣ እንዲሁም በማእድን ማውጣት ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ምድር-ባቡር ኮርፖሬሽን (...) ባለቤትነት እና በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (....) የሥራ ተቋራጭነት የሚካሄደው የወልድያ(ሃራገበያ) – መቐለ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው።
በኢ... የፕሮጀክቱ ሥራ ኣስኪያጅ ኣቶ ገብርመድህን ገብረኣሊፍ በቅርቡ ለመገናኛ-ብዙሃን እንደገልፁት የፕሮጀክቱ ስኬታማነት 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን የባቡር መጓጓዣ ሲጀምር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መስተጋብር ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ኣብራርተዋል። በተቋራጩ ኩባንያ ለተቋቋሙት ሰባት የማስተባበሪያ ቀጣናዎች እና በትግራይ ክልል በራያ-ዓዘቦ ወረዳ መቻረ ሜዳ ላይ የሚገኘው ኣንድ ዋና መስሪያ-ቤት በኣካባቢ ሚሊሻዎች፣ በመደበኛ ፖሊስ፣ እንዲሁም በፌደራልና በክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል ይጠበቃል። ፖሊሶቹ ልዩ ኣበል እየተከፈላቸዉ የጥበቃና የደህንነት ሥራ የሚያከናዉኑ ሲሆን በመብት ጥያቄና በተራ ኣምባጓሮ በሚፈጠሩ ግጭቶች ባገርቤት ዜጎች ላይ የድብደባና የማዋከብ በደል እንደሚፈፅሙ በርካታ የኣይን እማኞች ይገልፃሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቋራጩ ኩባንያ በተለይ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የፖሊስና የፀጥታ ባለሥልጣናት ዪፋዊ ያልሆነ ጉርሻ እንደሚሰጥ ሥማቸዉ ሊጠቀስ የማይፈልጉ የዉስጥ-ኣዋቂ ምንጮች ይጠቁማሉ።
ባገርቤት ሠራተኞች ላይ የሚፈፀም ግፍ ፈርጀ–ብዙ ነዉ። ለማስረጃነት ያህል ያነጋገርኳቸው የመብት ተጠቂዎች እንደተናገሩት ከሆነ የሠራተኛና ኣሰሪ ግንኙነት የጌታና የሎሌ የሆነ ያህል በንቀትና በስድብ የታጀበ ነዉ። የማዕድ ቤት ሰራተኞች ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ በቀን ከ16 ሰዓታት ላላነሰ ጊዜ ይሰራሉ። ለተቋራጩ ኩባንያ የፕሮጀክት የበላይ ኃላፊዎች የወሲብ ምቾት የሚተጉ ቆነጃጅት በኣዋሳቢዎች ይደለላሉ፤ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ከሥራ እስከ መባረር የሚደርስ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በቴክኒክ የሥራ መደብ የተቀጠሩ ሠራተኞች ሽንት ቤት እንዲያፀዱ ይገደዳሉ። ከሠራተኞች ደሞዝ ኣከፋፈል ጋር በተያያዘም በዘፈቀደ የተሰላ የሂሳብ ማጭበርበር እንደሚፈጸም ኣንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከኣፋር ክልል የተወከሉ የማህበራዊ ዋስትና ባለሥልጣን ቡድን በቅርቡ የመስክ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ኣንዷ የቡድኑ ኣባል ወይዘሮ እንባንቸዉን መቆጣጠር እያቃታቸዉ በኣይናቸው ያዩትን የህግ ጥሰት ኣጫዉተዉኛል። የቡድኑ ተልእኮ የኣገር-ቤት ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና መብት ምን ያህል ስለመከበሩ ማጣራት ነበር። እጅግ በርካታ ሠራተኞች የጥሮታ ዋስትና ማመልከቻ ቅፅ ኣልሞሉም ብቻ ሳይሆን ማህደር የተከፈተላቸውም ቢሆኑ ገንዘብ ፈሰስ ኣልተደረገላቸዉም። የቡድኑ ኣባላት እግረ-መንገዳቸዉን የዋስትና ማመልከቻ ቅፅ ማስሞላት ነበረባቸዉና ሠራተኞችን ኣንድ-በኣንድ እየጠሩ በማስሞላት ላይ እያሉ ቻይናዊው ኣለቃ ቅፅ በመሙላት ላይ ያለን ሰራተኛ በጥፊና በርግጫ እያጣደፈ ከወሰደዉ በኋላ ወዲያዉኑ ከሥራ ኣባርሮታል። "እንዲህ ኣይነት ግፍ በሃገራች እንዴት ይፈፅማሉ? ምን ያህል ቢንቁን ነዉ?” ሲሉ በኣንክሮ ይጠይቃሉ ወይዘሮዋ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሠራተኞች የመብት ጥያቄ ኣላነሱም ማለት ኣይደለም። ከተለያዩ ወረዳዎች የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳዉ ኣንድ ዓመት ከመንፈቅ በሆነ ጊዜ ዉስጥ የተቋራጩ ኩባንያ ከ500 የማያንሱ የመብትና የይገባኛል የክስ ጉዳዮችን ኣስተናግዷል። በተለይ የባቡር ሃዲዱ በሚያልፍባቸዉ የትግራይ ወረዳዎች የመብት ረገጣው የከፋ ብቻ ሳይሆን በህጉ መሰረት ለሰራተኞች መብት የፈረዱ ዳኞች በሌላ እንዲተኩ ተደርጓል የሚል ስሞታም ኣለ።
ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ ኣንፃር ከተቋራጩ ኩባንያ ወገን ስለዚህ የመብት ረገጣ ኦፊሴላዊ ኣስተያየት መጠየቅ ተገቢ ነዉ። ነገርግን ከንቱ ድካም ነው። እንኳንስ በመገናኛ-ብዙሃን ለሚወጣ ኣስተያየት፣ ይላሉ ኣንድ ኣስተያየት ሰጪ፣ በመደበኛ የሥራ ሂደት ላይ ካገርቤት ሠራተኛ ጋር የሚደረግ ማንኛዉም የመረጃ ልዉዉጥ መደበኛዉን የኣሰራር ሂደት የተከተለ ኣይደለም። ስለዚህ እንዲያዉ ዝም ነዉ። ለንፅፅር ያህል በቱርክ ኩባንያ 'ያፒ መርከዚ' በተያዘዉ ተመሳሳይ የምድር ባቡር ፕሮጀክት (አዋሽ – ሃራገበያ) ያለዉን ሁኔታ መዳሰስ ጠቃሚ ቢሆንም በዚህ ዘገባ ኣልተካተተም።
ኣሁን ምን 'ይጠበስ'?
ስለ የህግ የበላይነት፣ የዜጎች ደህንነት እና ስለ ብሔራዊ ሥነ–ምግባራችን የምንቆረቆር ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ኣንገብጋቢው ጉዳይ ይህ የመብት ጥሰት ብቻ ኣይደለም። ኢትዮጵያ ለፈረመችባቸዉ ዓለም-ኣቀፍ የሰብኣዊና የሰራተኞች መብት ስምምነቶች ፣ እንዲሁም በይፋ ላወጀችዉ የሰራተኛና ኣሰሪ ኣዋጅ 397/2003 ከቁብ የማይቆጥር ኢፍትሃዊ የሰዉ ኃይል ኣስተዳደር ሥርዓት በጠራራ ፀሃይ መተግበሩ ነዉ።
በኢትዮጵያ ምድር ይህ ሁሉ የመብት ረገጣ ሲፈፀም የህግ ዉክልና የተሰጣቸዉ በየደረጃዉ ያሉ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች፣ የፖሊስና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ለምን ድምፃቸውን ኣጠፉ? የሴራ መላምት እንጎንጉን ከተባለ ከቻይና የሥራ ባህል ኣንፃር እንደ ተራ ምግባረ-ብልሹነት የሚቆጠረዉ ጥቃቅን ሙስና (ፔቲ ኮረፕሽን) ተካሂዷል፣ ጉቦ ወይም ጉርሻ ተከፍሏቸው ሊሆን ይችላል ብለን መነሻ ልንይዝ እንችላለን። ይሁንና ተጨባጭ ምርመራ ያስፈልገዋል።
በጥቅሉ ሲታይ ግን ኢትዮጵያ የዉጭ-ቀጥታ-ኢንቨስትመንት በምታስተናግድበት ጊዜ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ለሚፈጥሩት ተፅእኖዎች መከላከያ ኣስቀድማ መላ መዘየድ ይገባታል። በደቡባዊ-እስያ ባሉ ሃገራት የተፈፀመዉን ኣይነት ወንጀል፣ ብዝበዛና ሥርዓት – ኣልበኝነት ለመከላከል የሚመለከታቸው በህግ ሥልጣን የተሰጣቸዉ ሁሉ ቅጥ ያለዉ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር ይገባቸዋል። በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (....) የተፈፀመዉና እየተፈፀመ ያለው ግፍ በተመለከተ ግን ኣስቸኳይና ዪፋዊ ምርመራ ተደርጎበት የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ ኣለበት። ኣልያም እንደነዚያ ተስፋቸዉ የተሟጠጠባቸው ያገሬ ሰዎች በዝምታ መቆዘም ከተመረጠ ቻይና ኢትዮጵያን በእጅ–ኣዙር ቅኝ እንደያዘች ልንቆጥረዉ እንችላለን።